Fana: At a Speed of Life!

የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማሸነፍና የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የክልሉ የመንግስትና የፓርቲ የስድስት ወራት አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር፥ እስካሁን በክልሉ ለመጣው ለውጥ በርካታ አመራሮች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር መክፈላቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም አሁን ያለው አመራር አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እንዲሁም ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳውን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ሲሉም ነው ያሳሰቡት።

ግምገማው ቀጣይ ጠንካራ ስራ ለመስራት የሚያግዝ በመሆኑ በግልፅና በጥልቀት ሊካሄድ ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፥ አመራሩ ስለፓርቲው በእኩል ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ ከግምገማው መድረክ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ጥንካሬና ክፍተትን በመለየት የመስራትና የማስፈፀም አቅምን ልናሳድግ ይገባል ያሉት አቶ ፍቃዱ፥ አመራር የሚመዘነው ችግርን በማውሳትና የተገኘውንም ጥቂት ውጤት በማጉላት ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሰላምና ልማት ማረጋገጥ ሲችል ነው ብለዋል።

እንዲሁም ለህዝባችን የገባነው ቃል መፈፀም አለብን ሲሉም ነው አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት።

አሁን ላይ እንደ ክልል የፖርቲውን የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት እየቀረበ ነው።

በአዳነች አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.