Fana: At a Speed of Life!

በሰላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ዓድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ” የሚል መሪ ሃሳብ በሰላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡

የሰላም ሚኒስቴርና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት መድረክ በሰላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ በንቅናቄው ወጣቶች በተለይም ከታችኛው የመንግስት መዋቅር ጀምሮ በሀገራዊ ማንነት፣ እሴቶችና ሀገራዊ ጥቅምን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፥ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያስመዘገቡት ድልና የገዘፈ ትርጉም ያለው ምንጊዜም የማይደበዝዝ ታሪክ ነው።

በመሆኑም ይህንን ደማቅ የታሪክ አሻራ የአንድነትና የአብሮነት መንፈስን በማጠናከር ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ወጣቶች ቀና እና ብሩህ አስተሳሰብን በመላበስ ለሰላም እና ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

በዛሬው የንቅናቄ መርሐ ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም የክልሎች እና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካዮች መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሀገር አቀፉ የወጣቶች ንቅናቄ እስከ ዓድዋ በዓል ዋዜማ ይቆያል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.