ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ ተደማጭነት እንዲጨምር ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤምባሲዎች አድማሱና አውዱ የሰፋ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
አቶ ደመቀ ዛሬ በተጠናቀቀው ዓመታትዊ የአምባሳደሮች ጉባኤ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የኤምባሲዎችን አድማስ ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት፣ ተደራሽ እና ተደማጭነት እንዲጨምር ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከሀገሮች ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኘነት እንዲጠናከር እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያችን እንዲሰፋ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
የአምባሳደሮቹ ጉባኤ መጠናቀቁን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የቀጣይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አስኳል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ተደራሽነት፣ ተደማጭነት እና ተፈላጊነት ማዕከል ያደረገ ስራ በቀጣይ እንደሚሰራ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር የሚኖራት የግንኙነት መርህ በብሔራዊ ጥቅም፣ በመከባበር እና ሽርክናን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዲፕሎማሲያችን ቁጥብ ሳይሆን ቀድሞ የሚደርስና ፈጣን እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አድማስና አውድ የማስፋት ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፥ አምባሳደሮች በዚህ ውስጥ የሚኖራቸውሚና ጉልህ እንደሆነ ተናግረዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቀሪው የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ መሰራት ስላለበት የዲፕሎማሲ ስራ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውም ተገልጿል።
በበረከት ተካልኝ