የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን 45 ቢሊየን ብር እዳ መክፈሉን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዕዳና የኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ከተረከበው 400 ቢሊየን ብር ዕዳ እስካሁን 45 ቢሊየን ብር መክፈሉን ገለጸ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ጌታሁን÷ በ2012 ዓ.ም 7 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ለማቃለል የሚያስችል ጥናት በማድረግ ካለባቸው 780 ቢሊየን ብር ዕዳ 570 ቢሊየን ብሩን መክፈል እንደማይችሉ መረጋገጡን አስታውሰዋል።
በዚህም ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ባለው ከ570 ቢሊየን ብር 400 ቢሊየኑን ብር መረከቡን ጠቅሰው÷ ኮርፖሬሽኑ እዳዎችን በተለያዩ አማራጮች እየከፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚመደብለት የትርፍ ድርሻ፣ ከፕራይቬታይዜሽን፣ በራሱ በሚያደርጋቸው የንግድ ሥራዎችና ሌሎች የፋይናንስ ምንጮች በሚያገኘው ገንዘብ ዕዳውን የሚከፍል መሆኑንም ገልፀዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ወደ ሥራ የገባው ኮርፖሬሽኑ ከተረከበው 400 ቢሊየን ብር ዕዳ እስካሁን 45 ቢሊየን ብር መክፈሉን ተናግረዋል።
ዕዳውን ለመክፈል ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ ባለፈው ዓመት የብድር ክፍያ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ መደረጉን ጠቅሰው፣ ለዚህም የተለያዩ የልማት ድርጅቶችን የማቀናጀትና የአሠራር ሥርዓቶችን በመቅረፅ ላይ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የቀድሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድን ተረክቦ እንዲያስተዳድር መደረጉንና እስካሁን ባለው የቦርዱን ንብረቶች በመሸጥ 100 ሚሊየን ብር ወደ ኮርፖሬሽኑ ገቢ መደረጉንም እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።
ለኮርፖሬሽኑ ሥራ ውጤታማነት የኃብት አስተዳደር ሥራ ወሳኝ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ለተቋሙ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።