የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ልዩ ልዩ ሐሰተኛ ሰነዶችንና ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩና የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የመንግስት ባለስልጣናትን ስም በማንሳት ”እነ እከሌን እናውቃለን፤ ጉዳያችሁን እንጨርስላችኋለን” በማለት የተለያዩ ሰዎችን በማጭበርበር ገንዘብ እየተቀበሉ ባለበት ወቅት ከማስረጃ ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ባለሃብትና ከፍተኛ ገንዘብ እንዳላቸው ለማስመሰል በርካታ የአሜሪካን ዶላር በሳምሶናይት ይዘው ፎቶግራፍ በመነሳት እና እራሳቸውን በማሳየት ሲያጨብረብሩ መቆታቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት የስራ ባልደረባ አባል ነን በሚል ሐሰተኛ መታወቂያ ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩና ሲያታልሉ እንደቆዩ ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አካባቢ በሚገኘው የአንደኛው ተጠርጣሪ ሞቱማ ደለሳ ቦሮቃ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ለወንጀል ተግባር ማስፈፀሚያ የሚገለገሉበት 90 ሺህ ብር፣ አንድ ሽጉጥ ከ24 መሠል ጥይቶች እና ከ2 ካዝና ጋር፣ አይፎንና ሳምሳንግ ሞባይል፣ አንድ አፒድ ላፕቶፕ እና ሦስት ፍላሾች ተይዘዋል፡፡
ህብረተሰቡ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በሚመለከትበት ጊዜ በማጋለጥ እና አሳልፎ ለፖሊስ በመስጠት እንዲተባበር የፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።