ብልጽግና ፓርቲ ኢኮኖሚውን እንዴት ገመገመው?
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ በ7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድርግ በማክሮኢኮኖሚ አመላካቾች መነሻ የስድስት ወሩ ግምገማ ማመላከቱን የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።
ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መደበኛ ስብሰባዎቹ በስፋት ከገመገማቸው ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚው ሁኔታ እንደሚገኝበት የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።
የማክሮኢኮኖሚ መዛነፎች፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር እና የምርታማነት ጉድለት የኢኮኖሚው ስብራቶች መሆናቸው ተለይቶ ባለፉት ዓመታት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
ኢኮኖሚው ዓለም ዓቀፋዊና ሀገራዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እያደገ እንዲሄድ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ያለፈው ዓመት የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እድገት 7 ነጥብ 2 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለያዩ ዘርፎች እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዘንድሮ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እድገት 7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአምራች ዘርፉ ባለፉት 6 ወራት 1 ነጥብ 07 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ታቅዶ 1 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ ምርቶችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
በአምራች ዘርፉ 368 ከፍተኛ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች በ37 ቢሊየን ብር ካፒታል ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ 421 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች በ47 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
የአምራች ዘርፉን የገንዘብ አቅርቦት ለማሻሻል እየተሰራ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ባለፉት 6 ወራት በዋና ዋና የማክሮኢኮኖሚ አመላካቾች መነሻ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው በተቀመጠው እቅድ መሰረት አፈጻጸሞች መኖራቸው እንደተገመገመ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ መቀዛቀዝ ቢታይም፤ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች በታህሳስ ወር መጨረሻ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም በሸቀጦች የወጪ ንግድ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።
በ6 ወሩ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው፤ የታህሳስ ወር አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።
ሆኖም በሚፈለገው ልክ የሀገር ውስጥ የስራ እድል መፍጠር እና የኑሮ ውድነት ጉዳይ አሁንም አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውንም ፓርቲው እንደገመገመ ተነስቷል።
በተለይ የሀገር ውስጥ ስራ እድል ፈጠራ አፈጻጸሙ 60 በመቶ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በዚህ ላይ ፓርቲው መምከሩንና ይህንን አፈጻጸም ለማሻሻል ውሳኔ አሳልፏል።
የዜጎችን ህይወት እየፈተነ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍም መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በምስክር ስናፍቅ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!