ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን በድንገት ተገኝተው ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚ እና ተመራጭ ለመሆን እየሰራ ያለውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር ) ከሰሞኑ በድንገት ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡
ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በየተቋማቱ ባልተጠበቀ ሰዓት እየተገኙ ሥራዎችን የሚገመግሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና መሥሪያ ቤት የተቋሙን አዳዲስ የማስፋፊያ ሥራዎች በመመልከት ነው ጉብኝታቸውን የጀመሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀድመው የተመለከቱት ሕንፃ ፋና ቴሌቪዥን በቅርቡ ወደ ሥራ የሚያስገባውን አዲስ ስቱዲዮ ነው፡፡
በዋናነት የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እና አሳታፊ መድረኮችን እንዲያስተናግድ ታስቦ የተገነባው ይኸው ስቱዲዮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተጨማሪ ጥንካሬን የሚያላብስ ነው፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሁሌም በእድገት ውስጥ እንዳለ የሚያመላክትም ነው፡፡
ፋና እስካሁን ድረስ ተወዳጁን ፕሮግራም ፋና ላምሮት ጨምሮ በርካታ ሰዎች የሚገኙበት የውይይት መድረኮችን ከዋናው መሥሪያ ቤት ውጭ በተከራየው ሕንፃ ነው ወደ ተመልካቾች እያደረሰ የቆየው፡፡
ሕንፃው ለሚዲያ ታስቦ የተሰራ ባለመሆኑ ግን ለሥራው በሚፈለገው ልክ ምቹ አልነበረም፡፡
ተቋሙ ለሕንፃ ኪራይ በየወሩ ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣትም ይገደድ ነበር፡፡
አዲሱ ስቱዲዮ ታዲያ ይህን ወጪ የሚያስቀርና ፋና በተሻለ አቀራረብ ወደ ተመልካቾቹ እንዲደርስ የሚያስችለው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ነባሩን የፋና ስቱዲዮ እና የሥራ ቦታም ተመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሐሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት የሚዲያው ዘርፍ አልፎም የሀገራት ዋነኛ ፈተና ነው፡፡
የሐሰተኛ መረጃው ፍጥነት እና አድማጭ ተመልካቹ ጋር የሚደርስበት መንገድ መብዛት ደግሞ ወቅቱን ይበልጥ ፈታኝ አድርጎታል፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የትርክት ችግር ባለበት ሀገር ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ችግሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማስቀረት መንግሥታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ ሪፎርም ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል ሚዲያ አንዱ ነው።
በመገናኛ ብዙኃን ላይ በተሰራው የሪፎርም ሥራ የወል ትርክቶችን ማጽናት የሚያስችል ተግባር መጀመሩን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ እየታየ እንዳለው ተቋማት እየተጠናከሩ ሲሄዱ አፍራሽ ሃሳቦች ቦታ እያጡ ይሄዳሉም ብለዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ከአዲሱ ስቱዲዮ እስከ ነባር የሥራ ክፍሎቹ ተዘዋውረው የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ባዩት ነገር እጅግ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይነትም ተቋሙ በፈጠራዎች ውስጥ ሆኖ እድገቱን በማፋጠን ሀገራዊ ተልዕኮውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡