ፋና በቀጥታ ከሀገራችን እና ከህዝባችን ጋር የሚገናኝ ሥራን ይዞ ይዘልቃል -አቶ አድማሱ ዳምጠው
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቀጥታ ከሀገራችን እና ከህዝባችን ጋር የሚገናኝ ሥራን ይዞ ይዘልቃል ሲሉ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ተናገሩ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን አዲስ የፋና ላምሮት ዘመናዊ ስቱዲዮ አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሃሐግብሩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ፣ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በሥነ -ሥርዓቱ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ፋና በሀገሪቱ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ በልዩነት ውስጥ የሚያምር ህብርን፣ ለስነ ልቦና መቀራረብና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከሪያነት አሻራ ማኖር ነው፡፡
ከአሰስ ገሰስ ፍሬ አልባ ሃሳቦች ይልቅ ጠንከር ያሉ የዜና እና ትንታኔ የስክነት እና እድገት ሃሳብ መርጦ፣ ሃሳብ ገዝቶ፣ ሃሳብ ሸጦ ፣የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሀገራዊ መልክ ኖሮት እና ተግባቦት ተፈጥሮ ብዝሃ ሃሳብን አስተናግዶ መሪ መሆን አልፎም ትርፋማነትን ማረጋገጥ የፋና ተልዕኮ እና ግቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመዝናኛው ዓለም የትውልድ መታያ እና መድመቂያ መድረክ ሆኖ ፣እድል ሰጥቶ፣ አሳትፎ ፣ኢንዱስትሪውን ማሳደግ፣ በሰው እና ሰውኛ አቀራረብ የሀገር ሰው እሴቶችን በሚጨምር የጥበብ ውጤቶች ማበረታቻ ማነቃቂያ፣እውቅና ሰጥቶ ሃገሩን አፍቃሪ፣ባህን አክባሪ፣ እድገትን አብሳሪ እድገትን አሻጋሪ እና አብሳሪ ትውልድ መፍጠርም ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ለጋራ ጎጇችን ማድመቂያ የሚታትሩ እጆች እንዲሰፉ ተሞክሮን መቀመር ፣ስራ ፈጣሪነትን ማበረታታት፣በተቃራኒው በተቋማት አፈፃፀም ሰንካላ አገልግሎት አሰጣጥ ምክንያት መልካም አስተዳደር ሲጓደል ደግሞ ለማጋለጥ ብቻም ሳይሆን ለማረም ፣ ለማፍረስ ሳይሆን ለመገንባት፣ ድክመቶችን እንዲተቹ እንዲታረሙ መስራት የ29 ዓመት ጉዟችን ማስታወሻ የዛሬነታችን መታያ እና የነጋችን ስንቅ ነውም ነው ያሉት አቶ አድማሱ ፡፡
ጉዟችን እንቅፋት አላጣውም ፣ፍላጎት ሲጨምር አቅርቦት ግድ አለ፣ አቅምን ፈተነ ያሉት አቶ አድማሱ ግን ፋና አንድ መለያና ልምድ አለው ፤ከፈተና ማግስት ድል ማብሰር ፤ “አንችልም አትበሉ ፣በትልቁ አስቡ፣ አቅዱ ፣በትንሹ ጀምሩ” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተምህሮ በተግባር በማሳየት ጠንካራና ብልህ በሆኑ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች አንችልም ወደ እንችላለን ተቀየረ ብለዋል፡፡
በትንሽ ጀምረን ፤ፋና በየዘመኑ ከሚመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር በፍጥነት እራስን የሚያስተዋውቅ ከመሆኑም ባሻገር 2 ብቻ የነበረው የቴሌቪዥን ስቱዲዮ በአጭር ጊዜ ወደ ስድስት አሳድጓል ነው ያሉት፡፡
ምቹ፣ ሳቢ እና የሚወደድ የስራ ቦታን መፍጠር በለውጥ ሂደት የተቋማት ግንባታ ምሰሶ ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው ይሕን መሰል ስቱዲዮ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መገንባቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ለስቱዲዮ ግንባታው አስተዋፅዖ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲሱ ስቱዲዮም ነገ ለምንሰራቸው ተስፋዎች ብዙ ይናገራል ያሉት አቶ አድማሱ÷ በቀጥታ ከሀገራችን እና ከህብረተሰባችን ጋር የሚገናኝ ስራን ይዘን እንዘልቃለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ለዚህም በየዓመቱ የምናካሂደውን የአድማጭ ተመልካች ጥናት መነሻ በማድረግ ተወዳጅ የሚዲያ ቅርፆችን አዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
ሚዲያ ያለ የአድማጭ ተመልካች ምንም ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው በተጓዝንበት 29 ዓመታት ታማኝ እና ንቁ አድማጭ ተመልካች አሉን፤ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አብራችሁን ስለነበራችሁ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
“አብራችሁን የምትሰሩ አጋሮቻችንም እንዲሁ አብረን እንቀጥል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው