Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመመከት ከፋና ጋር በቅንጅት ይሰራል- አቶ መሃመድ እንድሪስ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመመከት ከፋና ጋር በትብብር ይሰራል ሲሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ ተናገሩ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን አዲስ የፋና ላምሮት ስቱዲዮ በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተገኙተ አቶ መሃመድ እድሪስ ባደረጉት ንግግር÷የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚያይበት አንድ መነፅር አለው፤ እሱም ሚዲያዎች ከመስፋፋታቸው ጎን ለጎን ምን ያህል ሀገርን ያከብራሉ የሚለው ነው ብለዋል፡፡

ሀገርን ማክበር የሚገለፀው ደግሞ የሀገርን ሕግ በማክበር እንደሆነ ጠቁመው÷ከዚህ አንጻር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአርኣያነት የሚጠቅስ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ፋና ፕሮግራሞችን ከማዘጋጀት፣ ህዝብንና ተመልካችን ከማክበር ጎን ለጎን ሕግ ማክበር ላይ ቅድሚያ እንደሚሰጥም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም ምስጋና አቅርበው ሕግንና ሀገርን የሚያከብር ረጅም መንገድ ይጓዛል ነው ያሉት፡፡

ከቴክኖሎጂ ማደግ ጋር ተያይዞ ሀገርን በሀሰተኛ መረጃ እና በጥላቻ ንግግር ለማፍረስ እየተሰራ ያለ አደገኛ ዘመቻ እንዳለ ጠቁመው÷ ይህን መመከት የምንችለው ትክክለኛውን መረጃ በፍጥነት ለህዝብ በማድረስ ነው ብለዋል፡፡

ከጊዜው ጋር የሚፈጥን ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል፤ያንን በማድረግ ደረጃ አሁን ላይ ያለው ስቱዲዮም ሆነ ፋና እየታጠቃቸው ያሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር ተጣምሮ እሰራቸው ያሉ ጉዳዮች የሚበረታቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ሚዲያው ለሕዝብ ደራሽ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ ጉዳዮች ተደራሽ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በፋና ሁልጊዜም አዳዲስ ነገር ማየት የተለመደ ነው ያሉት አቶ መሃመድ÷ ለሚጠበቅበት ረጅም ጉዞም በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.