የሲቪል ማኅበራት በአማራ ክልል ላጋጠሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ላጋጠሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተቀናጀ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድርሻቸውን እንዲወጡ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።
“የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ለዘላቂ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ሀሳብ የመንግስትና የአጋር አካላት የትብብር፣ የአጋርነትና የድጋፍ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ በአማራ ክልል ከ170 በላይ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በ367 ፕሮጀክቶች በ30 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
ክልሉ በአንበጣ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት፣ በድርቅ እንዲሁም አሁን በውስጥ ግጭት እየተፈተነ መሆኑን ጠቁመው÷1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ችግሩ በመንግሥት አቅም ብቻ መፍታት የማይቻል በመሆኑም የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር በበኩላቸው÷አሁን ክልሉ ባለበት የፀጥታ ችግር ውስጥም ሁኖ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የደረሰባቸውን ችግር ለማቃለል ከ400 ሚሊየን ብር በላይ መድቦ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ዝናብ ዘግይቶ በመምጣቱና ፈጥኖ በመውጣቱ ምክንያት ድርቁ በመባባሱ ለዜጎችና ለእንስሳቱ የምግብና ምግብ ነክ አስቸኳይ ድጋፎችን ማድረግና የተጎዱ የውሃ አካላትን በመጠገን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በክልሉ ውስጥ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ መሰረት አድርገውና ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ