ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸለሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።
ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት ነው የተበረከተው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ በጣልያን የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች አባላት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በተገኙበት ሽልማቱን ተቀብለዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው መስክ ቁልፍ ኢንቨስትመንቶችን ያደረገች መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡
ለአብነትም በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ሥራዎችን በማከናወንና በዐበይት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቧ ተገልጿል፡፡