በየዓመቱ ከሚመዘገበው የካንሠር ህሙማን ሕክምና የሚያገኙት 12 ሺህ ገደማ መሆናቸው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው 77 ሺህ የሚጠጋ የካንሠር ህሙማን 12 ሺህ ያህሉ ብቻ ሕክምናውን እንደሚያገኙ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የመሠረተ ልማትና የማኅበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት፣ በሚፈለገው ልክ የሕክምና ባለሙያ አለመኖር፣ ለሕክምናው የሚውሉ ዕቃዎች ከውጭ ሀገር የሚገቡ መሆናቸውና ለግዥ ረዥም ጊዜ መውሰዱ፣ ብልሽት ሲያጋጥምም መለዋወጫ በቀላሉ አለመገኘቱ የሕክምናውን ተደራሽነት ውስን ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ወደ ሕክምና ከሚመጡት 75 በመቶዎቹ ህመሙ ውስብስብ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ይመጣሉ፤ ይህም የታማሚውን ታክሞ የመዳን ዕድል ይቀንሰዋል፤ ሕክምናውንም የበለጠ ውድ ያደርገዋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
በሚኒስቴሩ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራ አስፈፃሚ፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ መሪ ዶ/ር ሰላማዊት አየለ÷ በ24 የመንግሥት ሆስፒታሎች የመድኃኒት ሕክምና (ኬሞቴራፒ) እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሁለንተናዊ የካንሠር ሕክምና አገልግሎት÷ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ በሐዋሳ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ በአይደር ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በሐሮማያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሕክምናውን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው÷ በ30 ሚሊየን ዶላር ወጪ የካንሠር ሕክምና ማዕከላት ማስፋፊያ በጥቁር አንበሳ፣ ጅማ፣ ሐሮማያ፣ ሐዋሳና ጎንደር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
98 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው የሐዋሳ ማዕከል በሁለት ወር ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ እንዲሁም ግንባታው 90 በመቶ የደረሰው የጎንደር ማዕከል በአንድ ዓመት ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ መካከል ጥቁር አንበሳ፣ ጅማና ሐሮማያ የጨረር ሕክምና እየሰጡ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል የማህጸን በር ካንሠር ቅድመ ልየታና ሕክምና ከ1 ሺህ 300 በሚልቁ የመንግሥት ጤና ተቋማት እንደሚሰጥ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው