Fana: At a Speed of Life!

የሥራ ተቋራጮች በግንባታ ወቅት ቅድሚያ ለደኅንነት እንዲሠጡ ኮሚሽኑ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ ተቋራጮች የሕንጻ እና ሌሎች ግንባታዎችን ሲያከናውኑ በሠራተኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለደኅንነት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ላይ በሚገኝ ሕንጻ ላይ ባጋጠመ አደጋ የ32 እና 35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት የግንባታ ሠራተኞች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

አደጋው የተከሰተው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በግንባታ ላይ ባለ ሕንጻ ሲሞላ የነበረ አርማታና ብረት ተደርምሶ ሠራተኞች ላይ በመውደቁ መሆኑን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም የሟቾቹን አስከሬን ከተጫናቸው ፍርስራሽ ሥር በማውጣት ለፖሊስ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡

የግንባታ ሥራዎች በሚሠሩበት ጊዜ አሠሪዎችም ሆኑ ሠራተኞች አስፈላጊውን የደኅንነት መርሆዎች ሊተገብሩ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በግንባታ ሥራ ላይ ቅድሚያ ለደኅንነት ባለመሥጠት በ2015 የሥድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.