ፓርቲው በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ተገቢውን ስራ እየሰራ ነው – ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ተገቢውን ስራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ፓርቲው ለቀናት ባደረገው የማዕከላዊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የዘመነ መረብ ምንነት፣ መልካም እድል እና ፈተናዎቹን በተመለከተ ሰፊ ግምገማ ማደረጉን የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ወቅቱ ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀምና ባለመጠቀም መካከል በሚደረግ ውድድር ላይ የሚመሰረት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህንን በመገንዘብ ፓርቲው በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ተገቢውን ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
መረጃ በፍጥነት በሚዘዋወርበት ወቅት መረጃን የማዛባት እድል እየሰፋ የመጣበት ወቅት በመሆኑ ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ በእውነት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን በፍጥነት በመስጠት ረገድ ተጨማሪ ስራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
ፓርቲው ጊዜውን ባማከለ መልኩ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማት በማደራጀት እና በዘርፉ ብዙ የሰው ሃይል በማፍራት እየሰራ ባለው ስራ ከወዲሁ ውጤት መታየት መጀመሩንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የተደራረቡ እና የቆዩ ችግሮች ያሉ በመሆናቸው መግባባት ባልተፈጠረባቸው ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ እንዲደረስ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።