ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ላይ ትልቅ ስራ በመስራቷ ዕውቅናን አግኝታለች – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ላይ ትልቅ ስራ በመስራቷ ዕውቅናን ልታገኝ መቻሏን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሸለሙትን የከበረው የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማትን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሯ÷ ዕውቅናና ሽልማቱ የተገኘው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር እንደ ሀገር በምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ላይ ትልቅ ስራ በመስራቱ ነው ብለዋል፡፡
የተሰጠን ሽልማትና እውቅና ኢትዮጵያ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም በመስኖ ስንዴ፣ በሌማት ቱሩፋት እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት ማሳየት መጀመሩን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ገልጸው÷ ለዚህም በአዝዕርት ልማት ወደ 36 በመቶ እድገት መታየቱን ተናግረዋል።
በተለይም በስንዴ ምርት ካለፈው አመት ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ወደ 200 በመቶ የሚጠጋ ጭማሪ እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በሌሎች ምርቶችም ከአምናው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ መገኘቱንም ነው የገለጹት፡፡
የመሪዎች ቁርጠኝነት በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ቀላል አይደለም ያሉት ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግብርና በተጨማሪ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ህብረተሰቡን በማነቃቃት በርካታ ህዝብን ያሳተፉ ስራዎች እንዲሰሩ በማድረግ ስኬታማ ስራ ሰርተዋል ብለዋል፡፡
የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ የእውቅና ሽልማቱም ላሳኳቸው ስራዎችና በዘርፉ በቀጣይ ለሚሰሯቸው ስራዎች ብርታት የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እውቅናና ሽልማቱ እንደ ሀገርም ያለውን ብዥታ የሚያጠራ፣ ዜጎች በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያግዝና ሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በጋራ በሰሩት ቅንጅተዊ ስራ ይህ ስኬት በመምጣቱ እውቅናው እነሱም የሚጋሩት መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህ ዘርፍ የድርሻቸውን ለተወጡ ሁሉ ምስጋና ይገባል ብለዋል፡፡
እውቅናው ሀገሪቱ በምግብ ራሷን ለመቻል ላስቀመጠችው ርዕይ ተፈጻሚነት የዘርፉ ባለድርሻዎች ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡