ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዕውቅናና ሽልማት ያገኙት ላሳዩት አመራርና ቁርጠኝነት ነው – ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የተሰጣቸው የከበረው የፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ ሽልማት ላሳዩት አመራርና ቁርጠኝነት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ እንዲሁም በፋኦ የዕውቅና መድረክ ለመታደምና ንግግር ለማድረግ በጣሊያን ሮም እንደሚገኙ በመግለጽ ሃላፊዋ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ አሜሎኒ የተዘጋጀው የጣሊያን አፍሪካ ጉባኤ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ማሻሻያዎች እያደረገች እንደሆነ የጠቀሱት ቢልለኔ ስዩም፤ በተለይ ደግሞ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሸያ አጀንዳ ውጤት እየመጣ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አምስት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ግብርና መሆኑን አስታውሰው፤ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ እና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እንዲሁም ከስንዴ ልማት ጋር በተያያዘ በተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ ዕውቅና እያገኘች እንደሆነ ጠቁመዋል።
በግብርና ዘርፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ በጣም አመርቂ ውጤት እያገኘን ነው ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ፤ በፋኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሰጠው የከበረው የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማት ላሳዩት አመራርና ቁርጠኝነት እንደሆነ አስገንዝበዋል።