Fana: At a Speed of Life!

ከ70 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ለሚገነባ የክትባት ማምረቻ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ70 ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለሚደረግበት የክትባት ማምረቻ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዶ/ር ሊያ ታደሰ÷ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ብሎም የዉጪ ምንዛሪን ለማዳን ፕሮጀክቱ ያለዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት የበኩላቸዉን ላበረከቱት አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸዉ÷ ኮርፖሬሽኑ ለሀገር በቀል ኩባንያዎች የሚሰጠዉ ትኩረት ከፍ እያለ መምጣቱን ገልጸው በተለይም በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመገንባት ለአምራቾች አዘጋጅቷል ብለዋል።

አክለውም በዘርፉ አቅምና ፍላጎቱ ላላቸዉ ሀገር በቀልና የዉጪ ኩባንያዎች ኮርፖሬሽኑ ከምንግዜዉም በላይ ቀልጣፋ አሰራር ዘርግቶ እንደሚቀበል መናገራቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የሺልድቫክስ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ዙር ከ70 ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ተደርጎበት እ.አ.አ በ2027 ክትባቶችን የማምረት ተግባር እንዲጀምር ዕቅድ መያዙ ተነግሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.