Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት እነ ኤልቤቴል ሀብቴ ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የቀድሞ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር እነ ኤልቤቴል ሀብቴ ላይ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል የክስ ለመመስረት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለዐቃቤ ሕግ 15 ቀን ሰጠ።

ተጠርጣሪዎቹ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የቀድሞ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር ኤልቤቴል ሀብቴ፣ የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ፍቅሩ ኦላና እንዲሁም በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት ቅዱስ መስፍን፣ አማኑኤል መስፍንና ተክሌ ከቡ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ከ17 ነጋዴዎች ከውጭ ሀገር እቃ ለማስመጣት በሚል ከተወሰደ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ጋር ተያይዞ ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል እና ከማታለል ተግባር ጋር ተያይዞ በወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲከናወንባቸው ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ስራ ማጠናቀቁንና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ለመወሰንና ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ህ/ ቁጥር 109/1 መሰረት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የዐቃቤ ሕግ የክስ መመስረቻ ጥያቄን በመቃወም የተጠረጠሩበት ወንጀል ተራ መሆኑን ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በተፈፀመው የወንጀል ድርጊት ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን በመጥቀስ ዋስትናን በሚያስነፍግ እና ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ በከባድ የሙስና ድንጋጌ ሊከሰሱ እንደሚችሉ ገልጾ፤ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን 15 ቀናትን ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.