የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣልያን እየተካሄደ ካለው የጣልያን-አፍሪካ ጉባዔ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በጣልያን የኢፌዴሪ ኤምባሲ ባዘጋጀው መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርገው ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት የተዘጋጁ እና ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩ ትላልቅ የጣልያን ኩባያዎች ተሳትፈዋል።
በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቤሳ ÷ የውይይት መድረኩ የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት እድሎች ይበልጥ እንዲረዱ ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ባለሃብቶች ኢንቨስት በሚያደርጉበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ኤምባሲው በኢትዮጵያ ለሚኖራቸው የሥራ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
ከተሳታፊ ኩባንያዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሽ የሰጡ ሲሆን÷ ኮሚሽኑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ÷ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሀገራቱ ያላቸውን የኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ካላቸው ዕምቅ አቅም አንጻር ከጣልያን ኩባንያዎች ጋር የኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስር አካል ተደርጎ መሠራት እንዳለበትም በአጽንኦት ገልፀዋል።