Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታ ተቋማትን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላምና ፀጥታ ተቋማትን ለማጠናከርና ከሐሰተኛ ዘመቻዎች ለመከላከል አዳዲስ ሕጎችን የማዘጋጀት ተግባር ትኩረት መሰጠቱን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ጉባዔ በሰላምና ደኅንነት ላይ መክሯል።

በውይይቱም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የጸጥታ ችግር መስተዋሉ ተነስቷል፡፡

በመሆኑም ለፀጥታ ችግሮች ምክንያት ናቸው ተብለው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አረጋ ከበደ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የፖለቲካ ስልጣን ከሕዝብ ድምጽ እንደሚመነጭ በሕገ-መንግሥቱ በግልፅ መቀመጡን አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ አልፎ ግን የግል ፍላጎትን በኃይል ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ሥራ አስፈጻ ኮሚቴ አባል ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው÷ “ጽንፈኛ ቡድኖች የሀገሪቱ የመጨረሻው የሰላም ማስጠበቂያ ምሽግ የሆኑ ተቋማትንና አመራሮችን መልካም ስም በማጉደፍ ሥራ ተጠምደዋል” ብለዋል፡፡

ይህን ሥራቸውን ለመከላከልም ሕጎችን የማጠናከር ብሎም አዳዲስ ሕጎችን የማዘጋጀት ተግባር በፓርቲው ትኩረት ተሰጥቶት ምክክር እንደተደረገበት አንስተዋል፡፡

በጉባዔው ሰላም ትልቁ አጀንዳ ሆኖ እንደተመከረበት ገልጸው÷ መንግሥት አሁንም ለሰላማዊ ትግል ቅድሚያ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

 

በመራኦል  ከድር

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.