የሲዳማ ባህላዊ ፌስቲቫል መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ባህል ለአብሮነትና አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ የሲዳማ ባህላዊ ፌስቲቫል በሀዋሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ፌስቲቫሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስጀምረውታል።
ፌስቲቫሉ የሲዳማን የጥንት እውቀቶችና የሚጠቀማቸውን ባህላዊ መገልገያዎችን ለአለም ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን÷ የአፊኒ ፌስቲቫል አንድ አካል የሆነው ‘ዳኤ ቡሹ’ በማለዳ ተከናውኗል።
ዳኤ ቡሹ የሲዳማ ህዝብ የጥንት መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሆን÷ ጥንታዊ የእንግዳ አቀባበልና የፍቅር መግለጫ ተደርጎም ይወሰዳል ነው የተባለው፡፡
በመሆኑም ፌስቲቫሉ ይህን ባህላዊ ስርዓት ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው ተብሏል።
በፌስቲቫሉ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ የቀረቡ የሲዳማ ህዝብ መገልገያ የሆኑ ባህላዊ ቁሳቁሶችም ለእይታ ቀርበዋል።
በጥላሁን ይልማ