ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 25 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ባለፉት ሁለት ቀናት በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አረጋግጫለሁ ብሏል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ መስፍን አሰፋ÷ የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው በአቅርቦት ችግር ብቻ ሳይሆን ምርት የሚደብቁ እና የሚያከማቹ ነጋዴዎች በመኖራቸው መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ቢሮው ከ67 ሺህ በላይ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትል ማድረጉን ጠቁመው ÷ ከ6 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገው በመገኘታቸው የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል ብለዋል።
በሌላም በኩል ከወረርሽኙ መከሰት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት ለመፍጠር ምርት ያከማቹ ነጋዴዎች ላይ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ከሰሞኑ በመዲናዋ በቀይ ሽንኩርት እና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አቶ መስፍን አንስተዋል።
ከዚያም ባለፈ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩልም ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አክለዋል።
ሃላፊው አያይዘውም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሸማቹ ማህበረሰብ ጎን ለቆሙ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በቢሮው ስም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን÷በወረርሽኙ ለማትረፍ የሚጥሩ አካላት ግን ከኢሰብአዊ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ሸማቹ ህብረሰተብም የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎችን በ8588 ላይ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በፋሲካው ታደሰ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።