በአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር ለማስፈን መረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ አስተማማኝና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር ለማስፈን መረባረብ እንደሚገባ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።
አቶ ደሳለኝ የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ÷ እንደ ክልል ከተገባበት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመውጣት ባለፉት ወራት ከፌዴራልና ከክልሉ የፀጥታ መዋቅር ጋር በመሆኑ ውጤታማ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ከሕዝቡ ፍላጎትና መንግሥት ማሳካት ከሚፈልገው የሰላምና ደህንነት ግብ አንጻር አሁንም ብዙ መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ የሚገኙ ጽንፈኛ ሃይሎች አሁንም ባሉባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ ያመረተውን ለገበያ እንዳያቀርብ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይማሩ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ግንባታው እንዳይቀጥል የለየለት ሕዝብን የማጎሳቆል ተግባራትን ሲፈጽም የሚስተዋል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የጸጥታ ሃይሉ ጽንፈኛ ሃይሉ እንዳይስፋፋ፣ ጥፋቱን በመቀነስ ባለበት ቦታ ተወስኖ እንዲዳከም የመከላከልና ሕዝብን የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የፀጥታ ሁኔታ መለኪያ የሕዝባችን ሰላምና መረጋጋት ነው ያሉት ሃላፊው፤ ሕዝቡን ወደ ጉስቁልና የወሰደውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ሪፎርም ማድረግ ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሪፎርሙ ትልቁ ግብ ዓለም አቀፍ ፣ አህጉር አቀፍና ሃገር አቀፍ የፀጥታ ሁኔታውን የተረዳ፤ በገለልተኝነት ለዜጎች ደህንነት እና ለሕገ መንግሥቱ የቆመ የጸጥታ መዋቅር እንዲኖር ማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ የፖሊስና አድማ ብተና፣ የማረሚያ ቤቶች እንዲሁም የሚሊሻ መዋቅር ግባቸው ሰላምና ደህንነት በማስፈን የሕዝቡን ልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ ተቀናጅተው እንዲሰሩ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
በክልሉ በ155 የስልጠና ማዕከላት ለሚሊሻ፣ ለማረሚያ ቤቶች ፖሊስ፣ መደበኛ ፖሊስና አድማ ብተና አባላት ከነገ ጀምሮ ስልጠና መስጠት ይጀመራልም ብለዋል።
የጽንፈኛ ሃይሉን በማዳከም የክልሉን የፀጥታ መዋቅር መልሶ በማጠናከር ሂደት ክልሉ ያስተላለፈው የሰላም ጥሪም ዓላማው ጽንፈኞች ከገቡበት ፀረ ሕዝብ ተግባር ተላቀው ሰላማዊ የትግልን እንዲከተሉ አልያም ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ እንደሆነም ተገልጿል።
ዛሬም ሕዝብና መንግሥትን ይቅርታ ጠይቆ ለመመለስ የሚፈልግ ሁሉ በሩ ክፍት እንደሆነለት ተጠቁሟል።
በተደረገው የሰላም ጥሪ መሠረት ከ6 ሺህ በላይ የጽንፈኛው ቡድን አባላት የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው መመለሳቸው፣ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ “መንግሥትን እንክሳለን፤ ተሳስተናል” ብለው ተጸጽተው የክልሉን የጸጥታ መዋቅርን መቀላቀላቸው ተመላክቷል፡፡
በተፈጠረው የተሳሳተ ተግባቦት ከቀድሞው የልዩ ሃይል ሰራዊት ወጥተው ተበትነው የጠፉ የነበሩ ሃይሎች በተደረገው ተደጋጋሚ ጥሪ እንደገና ተሰብስበውና ጥፋተኝነታቸውን አምነው መንግሥት ወዳሰበው የሪፎርም አካል ለመቀላቀል ሥልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉም ተብሏል።
ካለንበት የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ ነጻ በመሆን በተሻለ አቅም ወደ ልማት ለመምጣት ሕዝቡ አስተዋይና አርቆ አሳቢ በመሆኑ እስካሁን ሲያደርገው የነበረውን አስተዋጽኦ እንዲያስቀጥል ጥሪ ተላልፏል።
የመንግሥት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላምና ደህንነት ሥራው የድርሻቸውን ሊወጡና ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባልም ተብሏል።
በደሳለኝ ቢራራ