በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ምርመራ ለማጠናቀቅ 10 ቀናት ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ምርመራ ለማጠናቀቅ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት 10 ቀናት ለፖሊስ ፈቀደ።
ተጠርጣሪው በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል።
ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ የታየው ተጠርጣሪው በዛሬው ቀጠሮ ችሎቱ ከዚህ በፊት ለፖሊስ በተሰጠው የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተሰሩ የምርመራ ውጤቶችን ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ተሰጥቶት በነበረው የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎችን መስራቱን በዝርዝር አቅርቧል።
ቀሪ ማለትም ባስከፈተው የቅድመ ምርመራ መዝገብ ላይ ምስክሮችን አስቀርቦ ማስመስከር የሚሉ ምክንያቶችን ጠቅሷል።
በጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ምስክሮች ቃል የመቀበል ስራ እንደሚቀረው የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው የተጠቀሱ ቀሪ ምስክሮችን ሊያባብሉ ወይም ሊያጠፉብን ይችላሉ በሚል ስጋቱን ገልጾ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ በመርማሪ ፖሊስ የቀረቡ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ”አሳማኝ አይደሉም” የሚሉ መከራከሪያዎች ተነስተዋል።
”ቀሪ ምስክሮች ሊያጠፉብን ይችላሉ በሚል ካለማሳያ የሚነሳ ጥያቄ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ሆነው መቅረብ የለባቸውም” በማለት ጠበቃቸው ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ጠበቃቸው የቀዳሚ ምርመራ በሚል ምክንያት ከዚህ በፊት ቀጠሮ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ለቀዳሚ ምርመራ በሚል ብቻ ዋስትና ለማስከልከያ ምክንያት ሆኖ መቅረቡ ስነስርዓታዊ አይደለም ብለዋል።
በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል በተነሱ መከራከሪያዎች ላይ ፖሊስ መልስ ሰጥቷል።
በዚህም ምስክር ሊያጠፉ እንደሚችሉ ማሳያ ሊቀርብ ይገባል በሚለው በጠበቃ የተነሳውን ክርክር በሚመለከት መርማሪ ፖሊስ ”ተጠርጣሪው ከዚህ በፊት በአራት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ እየተጣራ እንደነበር በመጥቀስ በዛ መዝገብ ምስክሮችን ያስጠፋ በመሆኑ ምክንያት የምርመራ መዝገብ ተዘግቶ ነበር” በማለት መልስ ሰጥቷል።
በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ የተሰሩ በርካታ ዝርዝር ስራዎችን ”ለችሎቱ ባቀረብንበት ሁኔታ ላይ” በተሰጣቸው ጊዜ ምንም ስራ አልተሰራም ተብሎ መጠቀሱ አግባብ እንዳልሆነ ገልጿል።
በተጨማሪም መርማሪው የተከፈተ የቅድመ ምርመራ መዝገብን በሚመለከት ”ለምስክሮች ደህንነት ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት በዐቃቤ ሕግ በኩል ጥበቃ ከተደረገ በኋላ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ስምምነት ላይ መደረሱን” ለችሎቱ አብራርቷል።
በፖሊስ የተሰጠውን መልስ ተከትሎ በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል ከዚህ መዝገብ ውጪ የተጠርጣሪውን የቀደመ ታሪክ በመጥቀስ ንፁህ ሆኖ እንዳይገመት ተጽኖ እየተፈጠረ ነው በማለት መቃወሚያ ቀርቧል።
በዚሁ ጉዳይ ቀደም ብሎ ትዕዛዝ መሰጠቱን በማስታወስ ጠበቃቸው በድጋሚ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም ምርመራው ያለበት ደረጃን አስቀርቦ የምርመራ መዝገቡን እንዲመለከትላቸው ጠበቃቸው ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የምርመራ መዝገብ ማጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ10 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ