በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የፍርድ ቤት ዳኛ ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የፍርድ ቤት ዳኛ ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ሰጠ።
ተጠርጣሪው የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዳኛ እና የፍርድ ቤቱ የኢንስፔክሽን ኃላፊ የሆነው ተስፋዬ ደረጄ፤ ከዚህ በፊት በሙስና ወንጀል ተከሶ የነበረ ሀብተማርያም ገ/መስቀል የተባለ ግለሰብን ጉዳይ የሚመለከቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች አብረውት እንደተማሩና እንደሚያውቃቸው በመጥቀስ እንዲሁም አንደኛውን ዳኛ “የስራ አለቃዬ ስለሚያውቀው ነጻ አወጣሃለው” በማለት በማግባባት የሙስና ገንዘብ ተቀብሏል ተብሎ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ሲከናወንበት ነበር።
ምርመራውን ሲያከናውን የነበረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን አስታውቋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ህ/ ቁጥር 109/1 መሰረት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል።
ተጠርጣሪው በበኩሉ የተጠረጠረበት የወንጀል ተግባር በሙስና ወንጀል ጉዳይ ሊታይ አይገባም በማለት በመከራከር ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲያከብርለት ጠይቋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ግለሰቡ የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ዋስትናን የሚያስከለክልና ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል በከባድ የሙስና ድንጋጌ የሚያስከስስ መሆኑን በመጥቀስ የተጠርጣሪው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደግ ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ