Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር ሊካሄድ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበር ከዓለም አቀፍ አሊያንስ ቦክስ ማኅበር እና ከሶሎ ኢንተርናሽናል ስፖርት ኃላ/የተ/የግል ማኅበር ጋር በመተባበር ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የአፍሪካ-ካናዳ ዓለም አቀፍ የቦክስ ፌዴሬሽን ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንስትራክተር ዮሴፍ ነጋሽ ÷ በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብሪታንያ፣ የኬንያ፣ የዩጋንዳና የአይቬሪኮስት ቦክሰኞች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል፡፡

በውድድሩ ታዋቂ ቦክሰኞች በአፍሪካ የከባድና የቀላል ሚዛን ሻምፒዮና የሆኑት ኮፊል ሚካኤል እና ዱኩ ሮናልድ በከባድ ሚዛን በ71 ኪሎ እንደሚወዳደሩና ኢትዮጵያም በከፊል ፕሮፌሽናልነት በ57 እና በ63 ኪሎ የምትወዳደር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሪካ-ካናዳ ዓለም አቀፍ የቦክስ ፌዴሬሽን ማኅበር ምክትል ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መላከ ተሰማ በበኩላቸው÷ ውድድሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ የሚካሄድ በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

ውድድሩ÷ በሀገሪቱ መካከል የስፖርታዊ አጋርነትንና የባህል ልውውጥ ለመፍጠር እንደሚያግዝ፤ በኢትዮጵያ መካሄዱም ተተኪና ፕሮፌሽናል የቦክስ ስፖርተኞችን ለማፍራት ብሎም የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ለመገንባትና በቦክሱ ስፖርት ዘርፍ መነቃቃት ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

ከውድድሩ ጎን ለጎንም ለቦክስ ዳኞች ስልጠናና ለፕሮጀክቶች ድጋፍ ይደረጋል መባሉን ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ውድድሩ “ሰላም በአፍሪካ” በሚል መሪ ሐሳብ መጋቢት 15 ቀን 2016ዓ.ም በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ከቀኑ 10 ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑን ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.