የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከኩባ አቻው አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሥራ ሀላፊዎች ከኩባ አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ የስኳር አምራች ኩባንያ የሥራ ሀላፊዎች ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዋዮ ሮባ ÷ በሸንኮራ አገዳ ባዮቴክኖሎጂ፣ በተለያዩ ምርቶች ልማት፣ በኦፕሬሽንና በጥገና አመራር፣ በመለዋወጫ አቅርቦት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ከኩባ ኩባንያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት ያለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለስኳር ልማት ያላትን እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀምና ዘርፉን ምርታማ ለማድረግ እንዲሁም የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት ኩባ በዘርፉ ልምድ ያላት በመሆኑ ይህንን ልምድ ቀምረን ዘርፉን ምርታማ ለማድረግ እንሰራለንም ብለዋል፡፡
መንግስት ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግል ለማዛወር እየሠራ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ረገድ ኩባ በዘርፉ ከሌሎች አገሮች ጋር በመስራት ያላት ልምድ ለኢትዮጵያም ጠቃሚ ግብዓት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ሁለቱ ወገኖች በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው መስኮች ተለይተው እንደሚቀርቡና በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት እንደሚፈረምም አብራርተዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኩባው ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር ቫልዴዝ ሜሳ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ውይይቱ እንደተካሄደ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መረጃ ያመላክታል፡፡