ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ተጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር፣ ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ጉብኝት አድርጓል።
በክልሉ ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በ400 ሚሊየን ብር እንዲሁም በገደብ ወረዳ በ123 ሚሊየን ብር እየተገነቡ የሚገኙ ሁለት ፕሮጀክቶች ናቸው የመስክ ምልከታ የተደረገባቸው።
የሁለቱም ፕሮጀክቶች አሁናዊ አፈፃፀም 90 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፤ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸው በጉብኝቱ ተመላክቷል።
ሃብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር፣ ዶ/ር) በመስክ ምልከታው÷ ፕሮጀክቶቹ ያለባቸው ችግር በአጭር ጊዜ ተፈቶ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።
በዚህም ከሶስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ በክልሉ 13 ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አንስተው፤ከእነዚህ መካከል የዲላ ከተማ እና የገደብ ወረዳ የንፁህ ውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሾቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሲሆኑ በዲላ ከተማ ለ192 ሺህ ሕዝብ ፤በገደብ ወረዳ ደግሞ ለ57 ሺህ ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማድረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በወንድሙ አዱኛ