Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሃብቷን ማካፈሏን እንደ ፀጋ ትመለከተዋለች – ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር፣ ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሃብቷን ለጎረቤት ሀገራት ማካፈሏን እንደ ፀጋ ትመለከተዋለች ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) ገለፁ።

ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በብዙ መልኩ ትስስር እንዳላት የገለጹት ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር፣ ኢ/ር)÷ሀብቶቿን በጋራ በመጠቀም የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ መስራቷንም ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሃብቷን ስታካፍል ተርፏት አለመሆኑን በመግለጽ አብሮ መልማትን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ማከናወን ስለምትፈልግ ነው ብለዋል።

ለጎረቤት ሀገራት በንፁህ መጠጥ ውሃና በኢነርጂ ሃይል አቅርቦት በኩል የምታከናውናቸው ተግባራት ለዚህ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸውም ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም በአዲጋላ-ጅቡቲ ፕሮጀክት አማካኝነት ኢትዮጵያ በየቀኑ 100 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃን ለጅቡቲ ለማቅረብ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተካፍላ እንደምትጠቀም የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በሶማሊያ በኩል የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ከኢትዮጵያ የማግኘት ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ይህን ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

ከመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተለያዩ የልማት መስኮች ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መስራቷ የህዝቦች ጉርብትናን ለማጠናከር እና የቀጣናውን የልማት ትስስር ለማጎልበት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በትብብር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ሚኒስትሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በመራዖል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.