በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2016/17 የምርት ዘመን የሚያስፈልገኝን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እያሠራጨሁ ነው አለ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ፡፡
ለ2016/17 የምርት ዘመን ለመስኖ፣ ለበልግ እና ለመኸር 1 ሚሊየን 476 ሺህ 546 ነጥብ 5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አድማሱ ወ/ማርያም አስታውቀዋል፡፡
የ804 ሺህ 670 ነጥብ 5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
የአፈር ማዳበሪያውን ወደ ክልሉ የማስገባት ሥራ መቀጠሉን ጠቅሰው÷ እስከ ጥር አጋማሽም 257 ሺህ 841 ኩንታል መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
እስከአሁን ከገባው የአፈር ማዳበሪያም 39 ሺህ 233 ነጥብ 5 ኩንታል ለመስኖና ለበልግ ወቅት እርሻ ግብዓት እንዲሆን መሠራጨቱን ነው ያስታወቁት፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን በበጋ መስኖና በበልግ ወቅት 484 ሺህ 792 ሔክታር መሬት በዘር በመሸፈን 65 ሚሊየን 644 ሺህ 442 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
በልግ ቀድሞ በሚገባባቸው አካባቢዎች የማሳ ዝግጅት ሥራ ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሩም በአቅራቢያው በሚገኙ ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው