በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ 420 ሺህ ሔክታር ለማልማት ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ420 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ የ2016 የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል፡፡
በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራው ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከተፋሰስ ልማት አንፃር ስምጥ ሸለቆ፣ ገናሌ ዳዋ እና ኦሞ ጊቤ በሚሰኙ ሶስት አበይት ተፋሰሶች ላይ እንደሚለማም ጠቁመዋል፡፡
በእነዚህ ተፋሰሶቸ ውስጥ በተለዩ 315 ዋና ዋና እና 7 ሺህ 713 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ አንደሚከናወን ነው ያመላከቱት፡፡
በዚህም 1 ሺህ 391 የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ልየታና ዲዛይን ዝግጅት በማጠናቀቅ ከ420 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
በቢቂላ ቱፋ