Fana: At a Speed of Life!

የ”ፀሐይ” መመለስ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በራሳችን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመተካት የሞራል ስንቅ ነው – ባለሥልጣኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ”ፀሐይ” አውሮፕላን መመለስ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በራሳችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመተካት የሞራል ስንቅ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

ባለስልጣኑ “ፀሐይ” አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አስመልክቶ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት÷ “ፀሐይ” አውሮፕላን በሀገራችን የአቪዬሽን ታሪክ ጉልህ ሚና ያላትና ከ87 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ምድር ተሰርታ የተሳካ የሙከራ በረራ ለማድረግ መቻሏን አስታውሷል፡፡

በዳግም የጣሊያን ወረራ ወቅት ወደ ጣልያን ተወስዳ በሙዚዬም ለዓመታት ተቀምጣ የነበረችው “ፀሐይ” አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ በመመለሷም የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

የ”ፀሐይ” ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ለአቪዬሽን ባለሥልጣኑ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑም አውስቷል፡፡

“ፀሐይ” የሀገራችን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ ተደርጋ እንደምትቆር ጠቁሞ÷ ኢንዱስትሪውን በራሳችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ለመተካት እየተደረገ ላለው ጥረት የሞራል ስንቅ እንደምትሆን አመልክቷል፡፡

ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡

የኤክስፖው ዋና አላማ ወጣት ተማሪዎቻች በሳይንስና ምርምር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ሀገሩን የራሱ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት በማድረግ ሀገራችንን የሳይንስ ውጤቶችን ገዢ ከመሆን ወደ አምራችነት እንድትሸጋገር ማድረግ መሆኑን የባለስልጠኑ መረጃ አስታውሷል፡፡

ስለሆነም ዛሬ የ”ፀሐይ” መመለስ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ አውሮፕላኗ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኩራትና ሃብት መሆኗን አስገንዝቧል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፀሐይ እንድትመለስ ላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.