ከ4 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ እንደ ሀገር ከተሰነዘሩ 4 ሺህ 623 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች 4 ሺህ 493 ያህሉን ማክሸፍ መቻሉ ተገለጸ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ የአሥተዳደሩን የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈፃፀምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷ በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት እንደሀገር 4 ሺህ 623 አጠቃላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መሰንዘራቸውን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 4 ሺህ 493 የጥቃት ሙከራዎች ወይም 98 ነጥብ 56 በመቶውን ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል፡፡
ከሳይበር ጥቃት ሙከራ 130 ያህል መከላከል ሳይቻል መቅረቱን ጠቁመዋል።
በመከላከል ሥራው ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የነበረ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
የከፍተኛ አደጋ ደረጃ ያላቸው የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸሩ በ115 በመቶ መጨመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ÷ የፋይናንስ ተቋማት፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የሕክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የድረገጽ ጥቃት፣ ማልዌር፣ የመሰረተ ልማት ቅኝት፣ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ፣ ሰርጎ የመግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡