በመዲናዋ የባህል ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ባህሎቻችንን ማወቅ፣ ስብራቶቻችንን መጠገን” በሚል መሪ ሀሳብ 15ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
ቢሮው ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ በዚህ የባህል ፌስቲቫል የማህበረሰቡን ወግና በጎ ማህበራዊ እሴቶች የሚያሳዩ የባህል ክዋኔዎችና ዝግጅቶች ይቀርባሉ።
የቢሮው የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ኩማ በመግለጫቸው÷ በፌስቲቫሉ የእደ ጥበብ ፈጠራ ምርቶችን የማስተዋወቅና የገበያ ዕድል የሚፈጠርበት መድረክ ይኖራል ብለዋል።
ከጥር 24 እስከ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም ለ3 ቀናት በጊዮን ሆቴል በሚካሄደው የባህል ፌስቲቫል ባህልን የተመለከቱ የውይይት መድረኮች፣ ሰርቶ ማሳያ አውደ ርዕዮች፣ የባህላዊ ጨዋታ ትዕይንቶች ይኖራሉ ተብሏል።
የክልል ከተሞችን ጨምሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በፌስቲቫሉ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የባህል መንደር ምስረታን ጨምሮ የአኗኗር ዘይቤ፣ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች፣ የሃገረሰባዊ ምግቦችና መጠጦች አዘገጃጀት እንዲሁም የተለያዩ ክዋኔዎች ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡
በመለሰ ምትኩ