በጋምቤላ ክልል ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በኢንቨስትመንት ዙሪያ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከመጡ ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
ባለሃብቶቹ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ሲሰሩ መንግስት ያስቀመጣቸውን ህግና መመሪያዎች ማክበር እንደሚጠበቅባቸውም አገንዝበዋል።
ባለሃብቶቹ በበኩላቸው÷ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የውሃ ሃብቶችን እንደጎበኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬትና በቂ የውሃ አማራጭ መኖሩን ተመልክተናል ማለታቸውን የክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ሥራ አንደሚጀምሩም ገልፀዋል፡፡