በሐረሪ ክልል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ሮዛ ኡመር ገለፁ፡፡
በሐረሪ ክልል ሲካሄድ የነበረው የ2016 ግማሽ ዓመት የመንግስትና የፓርቲ የስራ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተጠናቋል።
በመድረኩ ወ/ሮ ሮዛ ኡመር÷ ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ስራዎች መከናወናቸው ገልጸዋል።
ውጤት ከተመዘገበባቸው ስራዎች መካከል በክልሉ የፕሮጀክት አስተዳደር አቅምን ማሳደግ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የቱሪዝም ሀብትን በአግባቡ በማልማት ክልሉን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በተለይም የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ እንክብካቤ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ በመስኖ ልማትና የተለያዩ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀም በምግብ እራስን ለመቻል እና የግብርና ምርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በተለይም ከማምረቻና መሸጫ ቦታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው የገለፁት።
ገቢን ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘም በላቀ ትኩረት መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽ መረጃ ያመላክታል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው÷ አገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻልና መልካም አስተዳደር ከማስፈን አንፃር የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ እየታየ አለመሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ከመሬት አስተዳደር አንጻር ሕገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራዎች ላይ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ ይሰራልም ነው ያሉት፡፡