በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ የሚገኙ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ተጠቃሚና ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) የተመራ ልዑክ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ጋር በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ መክሯል፡፡
የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማፋጠን ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር ለፕሮጀክቶች መጓተት መንስኤዎች መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
በውሃው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራትን በቅንጅት በመሥራት ሕብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡