Fana: At a Speed of Life!

መልካ ቁንጥሬን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የዩኔስኮ ጉባዔ እየተጠበቀ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርኪዮሎጂ ሥፍራ የሆነውን መልካ ቁንጥሬ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ 46ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ ሣይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጉባዔ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

መልካ ቁንጥሬን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራትም መከናወናቸውን እና የዓለም ዓቀፍ ቅርስ መምረጫ ሠነድ ተሠናድቶ ለዩኔስኮ መላኩን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

ዩኔስኮ ግብረ-መልስ መስጠቱን እና የተቋሙ ገምጋሚ ቡድንም በመልካ ቁንጥሬ ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ማድረጉን በባለስልጣኑ የዓለም አቀፍ ቅርስ ሠነድ ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ ተስፋዬ አራጌ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የትግራይ መካነ-ቅዱሳን መልከዓ-ምድር (ገራዓልታ፣ አብረሃ ወ አጽበሃ፣ ዳንኤል ቁርቁር፣ ውቅሮና ሌሎችም) እንዲሁም የየሐ ባሕላዊ መልከዓ-ምድር በዩኔስኮ ጊዜያዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣዩ ዓመት ዓለም አቀፍ የቅርስ መምረጫ ሠነድ እንዲዘጋጅላቸው እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

የጣና ሐይቅ ደሴተ-ገዳማትና ባሕር ሸሽ መልከዓ-ምድር ዓለም አቀፍ የቅርስ መምረጫ ሠነድ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

የሠነድ ዝግጅቱን በያዝነው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

እንዲሁም የባሌ ድሬ ሼህ ሁሴን መስጂድ በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ሠነድ ተልኮ አስተያየት ተሰጥቶበታል፤ ክፍተቱ ተለይቶ በቀጣይ የማስተካከያ ሥራው የሚከናወንበት አግባብ እየታሰበበት ነው ብለዋል፡፡

ሶፍ ዑመር ዋሻም በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ሠነድ መላኩን አስታውሰው÷ በሠነዱ ላይ ዩኔስኮ አስተያየት መስጠቱንና ገምጋሚ ቡድንም ምልከታ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የሐላላ ኬላ፣ የሾንኬ መንደርና መስጂድ፣ የኤርታሌና ዳሎል በዓለም ቅርስነት ይመዝገቡልኝ የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ያነሱት አቶ ተስፋዬ÷ አንድ ቅርስ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት መከናወን ያለባቸው ተግባራትን ባለማጠናቀቃቸው ጥናት እንዲደረግባቸው በሚል ተመልሰዋል ብለዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.