የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርእይ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥር 2 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲካሔድ ታስቦ የተከፈተው የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርእይ እና ኤግዚቢሽን ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ አውደ ርእይ እና ኤግዚቢሽኑ የተራዘመው ጊዜ ሰጥቶ በትክክል ለጎብኝዎች ዕድል ለመፍጠር፣ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ተከትሎ የሚመጡ መሪዎችና ተወካዮች የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ በአውደ ርዕዩ ለማስመልከትና በዚህም የዲፕሎማሲ ግንኙነት አማራጭ ለማስፋት ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ የአፍሪካ መናኸሪያ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የዲፕሎማቲክና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛነቷ በዕድል ሳይሆን በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ ይህን ማስጠበቅ እና መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
ለ37ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ለማጠናቀቅ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሰሩ ስራዎች በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ከህብረቱ ጉባኤ ጎን ለጎን የሚደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚኖሩ ገልጸው፤ ባለፈው አመት በተከናወነው የህብረቱ ጉባኤ 50 ከሚሆኑ የሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች ጋር ስኬታማ ውይይት መካሄዱን አስታውሰዋል።
ዘንድሮም ይህ የሁለትዮሽ ውይይት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የህብረቱ ስብሰባ በስኬት መካሔድ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ስኬት በመሆኑ ሁሉም የተለመደ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በፍሬሕይወት ሰፊው