የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳያጋጥም እየሰሩ መሆኑን የሲዳማና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ገለፁ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ዳግም እንዳይከሰት በትኩረት እየሰሩ መሆኑን የሲዳማ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አስታውቀዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሬ ሞኬ ÷በምርት ዘመኑ ከ260 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስም 50 በመቶ ያህሉን የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ጽ/ ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ አዚዝ በበኩላቸው÷ ለማሰራጨት ከታቀደው 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ከ280 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው ብለዋል።
የ2016/17 የመኸር ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲሰራጭም ጠንካራ ክትትል ማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡
የቁጥጥር ሥራው ሕጋዊ ተጠያቂነት ያለው እና እስከታኛው መዋቅር ድረስ የሚሰራበት እንደሆነ የቢሮ ሃላፊዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን