Fana: At a Speed of Life!

በቦንጋ ለሚገነባው የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ለሚገነባው ለቶንጎላ ልዩ ሞዴል የ2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት ተቀምጧል፡፡

የመሰረት ድንጋዩን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) አስቀምጠዋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ ለሀገሪቱ ጠንካራ መሪ ለማውጣት ሁሉ ነገር የተሟላላቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት ከ8ኛ ክፍል በጣም ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች የሚማሩባት ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በ1 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ በመስከረም 2018 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን 250 ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር ሥራውን እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው ትምህርትን ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ እንዲጀመር የትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው አስተዋጽኦ ማመስገናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የትምህርት ስርዓት ስብራቱ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህንን ለመቅረፍ በየአካባቢው ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እና ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.