ባለፉት 6 ወራት በሬሚታንስ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት ተላከ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በሬሚታንስ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ መላኩ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር)÷ የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም 17 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 210 የዳያስፖራ ፕሮጀክቶች በክልሎች የመሬት አቅርቦት ተመቻችቶላቸው 21 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡
1 ሺህ 119 የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶችን በመክፈት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዳያስፖራ የሚገኘውን ሬሚታንስ ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትል ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደተላከ መናገራቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡