Fana: At a Speed of Life!

ኳታርና ሳዑዲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኳታርና ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር)÷ የኳታርና የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስታት ልዑካንን ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሳደግና በቅርበት ለመስራት ፍላጎት መኖሩ ተገልጿል።

ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ጠቁመው÷በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጠንካራ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢትዮ- ሳዑዲ ዓረቢያ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነት ቡድን ከሳዑዲ አምባሳደር ፏአድ አልሁማይዳኒ(ዶ/ር) ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡

በዚህም ሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ለሥራ የሚሄዱ ዜጎችን የመብት አጠባበቅና አያያዝ ላይ በጋራ መስራት እደሚገባ ተነስቷል፡፡

አምባሳደር ፏአድ አልሁማይዳኒ (ዶ/ር) ÷ የሀገራቱ ግንኙነት እጅግ የቆየና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዜጎችን መብት አያያዝና የሥራ እድል እንዲሁም የመብት አጠባበቅን በተመለከተ በጋራና ስምምነቶችን በማድረግ ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ማስረዳታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ተከታታይ ውይይትና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ችግሮችን ለመፍታትና ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.