Fana: At a Speed of Life!

የኮሪያ የሕክምና ልዑክ ለ6 ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኮሪያ የሕክምና ልዑክ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ህመም ችግር ላለባቸው ታካሚዎችን ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

15 አባላት ያሉት የህክምና ልዑኩ በሆስፒታሉ በመገኘት ሲወለዱ የልብ ህመም ለገጠማቸው ህጻናት ሕክምና በመስጠት የአምስት ቀናት ቆይታ አድርጓል፡፡

በሆስፒታሉ የልብና የደረት ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስትና የዩኒቱ ሐላፊ ዶ/ር አበበ በዛብህ÷ ሐኪሞቹ በሀገር ውስጥ ሊሰጡ የማይችሉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የልብ ሕመም ተጠቂ ለሆኑ 6 ህጻናት ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡

ህመሙ በአብዛኛው ጊዜ ህጻናት ሲወለዱ አብሮ የሚከሰትና ሕክምናው የሚሰጠው በከፍተኛ የሕክምና ባለሙያ በመሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል፡፡

የኮሪያ የሕክምና ቡድን ላለፉት 8 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተመሳሳይ ሕክምና ከሆስፒታሉ ሐኪሞች በጋራ ሕክምናውን ሲሰጥ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

በቀጣይ ይህ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንደሚሄድ መገለጹን የሆስፒታሉ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.