Fana: At a Speed of Life!

የጌዴኦ አባቶች ለዓለም ያበረከቱትን ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የመኖር ጥበብ ለማስቀጠል እንሰራለን – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጌዴኦ አባቶች ለዓለም ያበረከቱትን ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የመኖር ባህላዊ ጥበብ ለማስቀጠል አበክረን እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ አስተዋጾ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።

አቶ ጥላሁን በወቅቱ እንዳሉት÷ የጌዴኦ ህዝብ በባሌ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ፀጋን ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት የሚችልበትን ሥርዓት በመዘርጋት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዓለም እንዲማርበት ያደረገ ነው።

የጌዴኦ አባቶች በባህላዊ ሥርዓታቸው የሰው ልጅ እንዴት ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የሚኖርበትን ጥበብ ማኖራቸውን ገልጸው÷ ይህንን ጥበብ ለማስፋትና ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው÷ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዐ ምድር በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም አድርጓታል ብለዋል።

መንግስት በሰጠው ትኩረት አዳዲስና ነባር ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት፣ የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ስምና ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንዲበራከቱ በማድረግ ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንደ ጌዴኦ ባህላዊ መልክዐ ምድር ያሉ የቱሪስት መስህቦች በአግባቡ ለምተውና ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ እንዲተዋወቁና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚያከናውንም አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.