Fana: At a Speed of Life!

ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ግለሰቦች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈ

 

አዲስ አበባ፣ ጥ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ሥርዓት ባልተፈፀመባቸው ተሽከርካሪዎች ሐሰተኛ ሊብሬና ታርጋ በማውጣት ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላለፈ።

ተከሳሾቹ የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሰበታ ቅርንጫፍ ሠራተኛ የነበሩት ለሚ በየነ እና ያይላል ንጋቱ እንዲሁም በግል ሥራ የሚተዳደሩት መሪማ ጀማል፣ ጌታቸው ንጉሴ እና ቃልኪዳን አሰፋ ናቸው።

በተከሳሾቹ ላይ የኦሮሚያ ክልል የፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸው ነበር።

ክሱም÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 33 እና የሙስና አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2፣ አንቀጽ 33 እና የጉምሩክ አዋጅን አንቀጽ 167 ንዑስ ቁጥር 1፣ አንቀጽ 168 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 2 (ለ) ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነው።

1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በ2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሰበታ ቅርንጫፍ ባለሙያነት ሲሠሩ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ከሕግና አሠራር ውጪ የጉምሩክ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸው በአካል ባልቀረቡ ሦስት የV8 ተሽከርካሪዎች የታርጋ ቁጥር፣ ሊብሬና ቦሎ የተለያዩ የማረጋገጫ ሠነዶች እንዲወጣላቸው ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።

ጌታቸው ንጉሴና ቃልኪዳን አሰፋ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ የጉምሩክ ሥርዓት ያልተፈጸሙባቸው በተጠቀሱና ከሰበታ ቅርንጫፍ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ በሕገ ወጥ መንገድ የወሰዱትን የተሽከርካሪ የማረጋገጫ ሠነዶች ለባንክ በማቅረብ 26 ሚሊየን ብር ብድር መውሰዳቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ግለሰቦቹ ፈጽመዋል በተባለው ሕገ-ወጥ ተግባር በመንግሥት ላይ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በዐቃቤ ሕግ ተደራራቢ ክሶች ተመስርቶባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም በማለት የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ስድስት የሰው ምስክር ቃልና የተለያየ የሠነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱባቸው ድንጋጌዎች እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም÷ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መንገድ መከላከል ባለመቻላቸው ተከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.