Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኩባ በስኳር ዘርፍ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኩባ በስኳር ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኩባ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር ቫልዴዝ ሜሳ በቅርቡ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ነው የተፈረመው፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ እና የኩባ አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ ዋና ዳይሬክተር ፍራንሲስኮ ሬኔ ማርቲን ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ወገኖች በምርምርና ልማት ዘርፍ፣ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ፣ በፋብሪካና እርሻ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በሸንኮራ አገዳ ዝርያ ልማት፣ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በባዮቴክኖሎጂና በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በዘርፉ ንግድ በጋራ እንደሚሰሩ ተመልክቷል፡፡

አቶ ወዮ ሮባ÷ ኢንዱስትሪውን አሁን ካሉበት ተግዳሮቶች በፍጥነት ለማውጣት ኩባ በዘርፉ ያላትን የዳበረ ልምድ ለማካፈልና ከግሩፑ ጋር በትብብር ለመስራት ላሳየችው ፍላጎት አመስግነዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ተቋማቸው ቁርጠኛ እንደሆነ መናገራቸውንም የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ጆርጅ ሌፌብሬ በበኩላቸው÷ የስምምነቱ ቀጣይ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ተጠናቅቀው በፍጥነት ሥራ እንደሚጀመር አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.