በኦሮሚያ ክልል 253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከመኸር እርሻ እስካሁን 253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ እንደገለጹት÷ የክልሉ መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያዘጋጀውን ዕቅድ በፍጥነት እና በጥራት ፈጽሟል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥም የመኸር እርሻ አፈጻጸሙ ከተቀመጠው ግብ በላይ መሆኑን አንስተዋል።
በ2015/2016 የግብርና ሥራ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ 9 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ነው ሃላፊው የገለጹት፡
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር ማልማት መቻሉን ጠቁመው÷ ከዚህም 105 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።
በመንግስት በጀት ከሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ተሳትፎ በዜግነት አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራትም መልካም ውጤት እንደተገኘባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ስብራቶችን ለመጠገን የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ማስፋፋት ላይ በትኩረት ተሰርቷል ብለዋል፡፡
ከህብረተሰቡ በተሰበሰበ 65 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብም የቅደመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ እና አዳዲስ ግንባታ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን በሽብር ቡድኑ ሸኔ ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሽን እያካሄደ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት የተዘረጋለትን የሰላም ጥሪ ችላ በማለት ፀረ ሕዝብ ትግል ማድረጉን ቀጥሏል ያሉት ሃላፊው÷ በንፁሃን ሕይወትና ንብረት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሩም ለዚህ ግብሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ም የሸኔ ሽብር ቡድን በሕዝብ ውስጥ ፍርሃትን ለመንዛት እየሞከረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በክልሉ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን በማስቆም ፍላጎቱን በሃይል ለማስፈፀም የጠራው አድማ በሕብረተሰቡ እና በፀጥታ ሃይሉ ተሳትፎ ሊከሽፍ ችሏል ነው ያሉት፡፡
መንግስት ለሰላም የዘረጋው እጅ አሁንም አልታጠፈም ያሉት ሃላፊው÷ ይህን አሻፈረኝ ብሎ ክልሉን የጦር አውድማ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ እና ለዚህ ዕኩይ ተግባር የሚተባበር አካል ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ሰላሙን ለመጠበቅ ከመንግስት እና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል።
በሌላ በኩል ሕብረተሰቡ በተመጣጠነ ዋጋ መድሃኒቶችን ማግኘት እንዲችል 87 የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ 11 ዞኖች፣ 7 ከተሞች እና 83 ወረዳዎች ላይ ተስተውሎ የነበረውን የኮሌራ በሽታ በ5 ዞኖች፣ 5 ከተሞች እና 55 ወረዳዎች ላይ ስርጭቱን መግታት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በመራኦል ከድር