አየርላንድ በኢትዮጵያ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብሪና ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
አምባሳደር ኒኮላ ብሪናን በበኩላቸው÷ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ የሚሰጠውን ድጋፍ ከሚኒስቴሩ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በተመሳሳይ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የዩ ኤን ውማን የኢትዮጵያ ተወካይ ሲል መኩሩቡጋ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም በስርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ሴቶች ማብቃት ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡