አግሮ ኢንዱስትሪዎች በተሻለ መንገድ በሚደገፉበት የአሰራር ማሻሻያዎች ዙሪያ ስምምነት ላይ ተደረሰ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተሻለ መንገድ ለመደገፍ በሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ዙሪያ ስምምነት ላይ መደረሱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ፋቱ ሀይድራናን ጋር አግሮ ኢንዱስትሪዎችን በተሻለ መንገድ በሚደገፉበት የአሰራር ማሻሻያ ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገኙበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንደሌላቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ እንደማሳያነትም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጠቅሰዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተቋቋሙበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር የጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት እንዲኖራቸው ለማስቻል የኢንተርፕራይዝ ድጋፍ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በፓርኮች ውስጥ በብዙ ዘመናት ሰልጥነው ዘርፈ ብዙ እምቅ እውቀቶች ካካበቱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ የወጡ ዜጎች እውቀታቸውን ተጠቅመው ስራ መስራት እንዲችሉ ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ እውቀት ያላቸውን መሰል ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ደግፎ ወደ ስራ መመለስና የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲፈጥሩ ማስቻል ሀገራዊ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ሥራ ፈጣሪዎቹ የሚፈጥሩት ጥቃቅንና አነስተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገባውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብዓት አቅርቦት ችግርን እንደሚፈቱ ማሰብና መስራት አስፈላጊ መሆኑን ማመላከታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡